በዚህ ወቅት ምን ዓይነት ጋዜጠኝነት ይጠበቃል?
28/02/2013…….FG
የኔፓል ተወላጅ የሆነው ኩንዳ ዲክሲት በ1996 ዓ.ም. በሃገሩ ተከስቶ የነበረውን ጦርነት በፎቶ ጆርናሊዝም አጠናቅሮ በአውደ ርእይ መልክ ዲሴምበር 2010 ኒውዝላንድ ለእይታ አቅርቦ ነበር፡፡ በአውደ ርእዩ ላይ እንዲህ የሚል ሃሳብ ተናግሮ ነበር፡፡
“ይህ ጦርነት የኔ የሚሞተውም የኔ ወገን ነበር፡፡ የጋዜጠኝነት ትምህርት ጣልቃ አንዳንገባ አስተምሮናል፡፡ በቃ ተመልካች እንድንሆን ሰብኮናል፡፡ ሃገሬ ላይ በሚከናወን ጦርነት ግን ይህንን መፈጸም አልቻልኩም፡፡ እንዴት ይሆናል? ከጦርነት ሜዳ ውሎ፤ አለፍ ብሎ ለሰብአዊ ጥፋቱ ማሰብ ያስገድዳልና ” (ዲክሲት፡2010) አለ፡፡ ሆኖም ግን እርሱ እና እርሱን መሰል ዘጋቢዎች፣ በጦርነቱ ወቅት ከጋዜጠኝነትም በላይ የሰላም አምባሳደርነት ሚና እንደነበራቸው ለተመልካቾች ገለጻ አድርጎላቸዋል፡፡ የዚህ ምክንያቱ የሰላም ጋዜጠኝነትን (Peace Journalism) በመተግበራቸው እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
“ጋዜጠኝነት በሰዎች ደም የሚነግድ፣ ፊሽካ እየነፋ ግጭትን እንደ ኳስ ጨዋታ ዳር ሆኖ የሚያሟሙቅ እና ከመስዋእትነት የሚያተርፍ መሆን የለበትም” (ሊንች፡2012) የሚሉት ባለሙያው ጄክ ሊንች ጋዜጠኛ ለሰላምና ለሰላማዊ መፍትሄ መስራት እንዳለበት ያስረዳሉ፡፡ እ.ኤ.እ በ1974 የሰላም ጋዜጠኝነትን(Peace Journalism) ለመጀመሪያ ጊዜ ለአለም ያስተዋወቁት ፕሮፌሰር ዮሐን ጋልቱንግ በበኩላቸው የጦርነት ጋዜጠኝነትን(War Journalism) ሰብአዊነት የጎደለው፤ አሸናፊነትና ተሸናፊነት ብቻ ጉዳዩ የሆነ፤ በጉልበተኞች ተጽዕኖ ስር የወደቀ በማለት ይተቹታል (ጋልቱንግ፡ 2002)፡፡ በመሆኑም “የሚጻፈው ከመጻፉ፤ የሚባለው ከመባሉ በፊት ዘገባቸው የሚኖረውን ማህበራዊ ተጽዕኖ ጋዜጠኞችና ኤዲተሮች ቆም ብለው ማሰብና መምረጥ ይገባቸዋል” (ጋልቱንግ፡ 2002) ይላሉ፡፡

Comments
Post a Comment